ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የገንዘብ ሚኒስቴር የክልሉን የአስቸኳይ ጊዜ መልሶ ማገገሚያ እቅድ በጋራ ይፋ አደረጉ፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የገንዘብ ሚኒስቴር አመራር የትግራይ ክልል አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን ለመገምገምና ለማፅደቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀሌ ከተማ ሰፊ ምክክር ማድረጉ ተገልጿል።
በምክክሩ ወቅት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆንን ለመቀነስ በፍጥነት የማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን አስቀድሞ መጀመር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር አብርሃም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የክልል ቢሮዎች የመልሶ ማገገሚያ እቅዱን ሙሉ በባለቤትነት እንዲወስዱ እና አተገባበሩን እንዲጀምሩ አሳስበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሃብሪቢ በበኩላቸው እቅዱ የተዘጋጀው በክልሉ በደረሱ ጉዳቶች እና በአስቸኳይ ጊዜ መልሶ ማገገሚያው ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ግምገማ ከተደረገ በኋላ ነው ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚሁ የግምገማ ሂደት ላይ ከፌዴራል፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ከተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች፣ ከዩኤስኤድ፣ የቴክኒክ ልማት አጋሮች፣ ከዓለም ባንክ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።
አያይዘውም ዕቅዱ መንግስት የሰብዓዊ ጥረቶችን ከግብ ለማድረስ በኢኮኖሚ ማገገሚያ እና ለሰላም ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ዕቅዱን ለማበልፀግ እና ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ምንጮች ሀብት ለማፈላለግ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ ምክክር እንደሚደረግ ተጠቁሟል ፡፡