ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት ውጤታማ፣ ፍትሃዊና ለእድገት ጥቅም ለማስገኘት ማልማት ያስፈልጋል – ዶ/ር ስለሺ በቀለ

 

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት ውጤታማ፣ ፍትሃዊና ለእድገት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል መንገድ ማስተዳደር እና ማልማት ያስፈልጋል ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የውሃ አካል ዳርቻ ክልልን ለመወሰን የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለማዳበር የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የፌደራል እና ክልል ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ተመራማሪዎች እና ምሁራን በተገኙበት በቢሾፍቱ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ከውሀ ሀብት ተገቢውን ጥቅም እና ግልጋሎት ለማግኘት የውሃ ሀብት ግኝት ከጥራትም ከብዛትም አንፃር አስተማማኝ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ለዚህም ውሃና የውሃ አካላትን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የውሃ አካል ዳርቻ ክልልን የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በተለይ የውሃ አካላት ዳርቻን በመጠበቅ ሂደት ውስጥ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የውሃ አካላቱን ከብክለትና መሰል ችግሮች መከላከል ለነገ የማይባል የቤት ስራ መሆኑን አመልክተዋል።

የውሃ አካል ዳርቻ ክልልን ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በየደረጃው ለባለድርሻ አካላት ለውይይት መቅረቡ እና ረቂቁን አዳብሮ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት መካከል ከልክ በላይ የሆኑ የንጥረ ነገር ክምችቶችን፣ በደለል የመሞላት፣ በመጤና ተስፋፊ አረሞች የመወረር እና የብዝሃ ህይወት መመናመን ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆናቸው ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ በልዩ ልዩ ግብዓቶች ዳብሮ ተግባራዊ ሲሆን፣ በሀገሪቱ በሚገኙ በማናቸውም የውሃ አካላት ማለትም ሀይቆች፣ ግድቦች፣ ወንዞች፣ ረግራጋማ ቦታዎች እና የከርሰ ምድር ውሃዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
(በደረሰ አማረ)