ሀገሬ-“ጦሳ ዞኮ” – የእግዜር ድልድይ


የእግዜር ድልድይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የሚገኝ ድንቅ የመስህብ ሥፍራ ነው።

ድልድዩ በቱሪዝም መዳረሻነቷ ከምትታወቀው ከአርባ ምንጭ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድልድይ በአባያና ጫሞ ሀይቆች መካከል ያለ የመሬት አካል ነው።

በሁለቱ ውሃ አካላት መካከል የሚገኘው ይህ የመሬት ክፍል በአካባቢው አጠራር “ጦሳ ዞኮ” ወይም የእግዜር ድልድይ ይባላል።

የሰው ልጅ የፈጠራ ሥራ ያልታከለበት ፈጣሪ አመቻችቶ የሠራው ነው ሲሉም ነው ይህንን ሥፍራ “ጦሳ ዞኮ” ብሎ የጠሩት።

ከአርባ ምንጭ ተነስተው ወደዚሁ እግዜር ድልድይ ሲጓዙ በአረንጓዴና ነፋሻማ አየር ከተጎናጸፈው ጥብቅ ደን የሚነፍሰው ንጹህ አየር ይቀበሎታል። በጉዞዎም ግራ ቀኞዎን የሚያዩት የተፈጥሮ ትዕይንትና የሚያገኙት ንጹህ አየር አእምሮዎን ያድሳል።

ወደ እግዜር ድልድይ ከፍታ ላይ ሲደርሱ የተጎናጸፋቸው የብዘኃ – ሕይወት ስብጥርና ድንቅ መስብህነቱ በሐሴት ይሞላዎታል።

የነጭ ሣር ብሔራዊ ፖርክ አካል የሆነው ይህ የመሬት አካል አብዛኛው በሣር የተሸፈነና አልፎ አልፎ ዛፎችና እና ቁጥቋጦዎች የሚገኝበት ነው።

ድልድዩ ከአባያ ሀይቅ እስከ ጫሞ ሀይቅ አራት ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ የሜዳ አህያዎች ወይም የዜብራዎች መኖሪያም ሲሆን በዚሁ የመሬት አካል ከፍታ ላይ ሆነው የተንጣለለውን የነጭ ሣር ውበት ቁልቁል ተመልክተው ሐሴትን ይጎናጸፉሉ።

ከዚሁ ባሻገር ከእግዜር ድልድይ ሆነው ግራና ቀኝ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ድንቅ ውበት እስከ ዓይንዎ ዕይታ ጥግ ድረስ ይቃኙታል። የሁለቱን ሀይቆች ቀለምና ውበት እንዲሁም ስፋት የሚመለከቱት ከዚሁ ከተፈጥሮ ድልድይ በመሆኑም በተፊጥሮ ውበት ይደመሙበታል።

ሁለቱ ሃይቆች በስፋት፣ በጥልቀት እና በቀለም የተለያየ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ የጫሞ ሀይቅ 550 ኪ.ሜ ስኩዌር ስፋት ከ6 እስከ 13 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው አባያ ደግሞ 1ሺሕ 160 ኪ.ሜ ስኩዌር ሲሸፈን ጥልቀቱ በአማካይ 13 ሜትር መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በድንቅ ተፈጥሮ የታደለው የጋሞ ዞን ታይተው የማይጠገቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባለቤት ነው፡፡ የጉጌ ተራራ፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ ለአርባ ምንጭ ከተማ ስያሜ መነሻ የሆኑ አርባ ምንጮች፣ የአዞ እርባታ እና የአዞ ገበያ እንዲሁም ሌሎች ባህላዊና ታሪካዊ መስህቦች በዞኑ ይገኛሉ፡፡

ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ሲመጡ በውስጧና በአካባቢዋ የሚገኙትን ውብ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ መስህቦችን ይጎበኛሉ፡፡ አርባ ምንጭን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ