በኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሳው የቤተ ክርስቲያኗ ሕንጻ የመልሶ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሳውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕንጻ የመልሶ ግንባታ ሥራን አስጀመሩ።

በእለቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የከተማ ፕላን እና ልማት እንዲጠበቅ፣ ከተማችን እንድትለማ፣ እንድትዘምን እና የተሻለ ዲዛይን እንዲተገበር በርካታ ትብብር በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን ይህ ዛሬ መልሶ ግንባታ ስራውን ያስጀመርነው ሕንጻ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው” ሲሉ በማኅበራዊ የትስሰር ገጻቸው አስፍረዋል።

ዛሬ በይፋ የተጀመረው ይህ ግንባታ ለመኪና ማቆሚያ ግልጋሎት የሚውል አንድ የምድር ቤትን ጨምሮ ዘመናዊ ባለ አራት ወለል ሕንጻ መሆኑ ተጠቅሷል።

አዲሱ ሕንጻ ከአካባቢው ልማት፣ ፕላን፣ በዙሪያው ካሉ ሌሎች ቅርሶች እንዲሁም ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ጋር የተናበበ ኪነ ህንጻ ይኖረዋል ተብሏል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች የልማት ኮሪደር ስራውን በመደገፍ ከጎናችን ስለቆሙ ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፤ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን ለቤተክርሰቲያኗ የምናስረክብ ይሆናል ብለዋል።

በግንባታ ማስጀመሪያው ስነ-ስርዓት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክን ጨምሮ ሌሎች የሀይማኖቱ አባቶች እና የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

አዲሱ ሕንጻ የሚገነባው በተለምዶ የማህሙድ ሙዚቃ ቤት ይባል በነበረውና በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማት ምክንያት በፈረሰው ህንጻ ላይ ነው።