ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ስርዓት ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል – የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ

ሚያዝያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ስርዓት ለመገንባት እንዲሁም የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና እርካታን ለማረጋገጥ ባለፉት 9 ወራት በየደረጃው በሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ መዋቅሮች በርካታ ስራዎች መከናወኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህንነ ያሉት የብልጽግና ፓርቲ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በመክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽሕፈት ቤቱ የዘርፍ ኃላፊዎች እና የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩም የውስጠ ዴሞክራሲ ባህል ደረጃ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገኙ የለውጥ እመርታዎችና በምርጫ ማግስት ፓርቲው ለሕዝቡ ቃል የገባቸው ጉዳዮች የተፈፃሚነት ደረጃ ትኩረት እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአምስቱ ሀገራዊ የልማት የትኩረት መስኮች የተገኙ ውጤቶች፣ የብሔራዊነት ትርክትን እንደ ሀገር ለመገንባት የተሄደባቸው ርቀቶች እንዲሁም የ2ኛ መደበኛ ጉባዔ ዝግጅትም ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡

መድረኩ የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ በመገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየትና የተግባራትን ስኬታማነት በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝም ነው ያስረዱት፡፡

እንዲሁም ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ በዘርፎች የተከናወኑ የዘጠኝ ወራት ሪፖርት፣ የተጠናቀቁ የፓርቲ መመሪያዎች እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ቅድመ ዝግጅት መነሻ አቅጣጫዎችም እንደሚቀርቡ ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።