ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች የተሻለ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛሉ፤ ጠላቶቻችን ይህንን ሊረዱ ይገባል- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) በአሁኑ ወቅት ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች የተሻለ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛሉ፤ ጠላቶቻችንም ይህንን በውል ሊረዱ ይገባል ሲሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በባሕርዳር ከተማ በተካሄደው የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች የእውቅናና የምስጋና መርኃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግርም በአሁኑ ወቅት የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በተሻለ አቋምና ብቃት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የእነዚህ ኃይሎች የተሻለ ብቃትና አቋም ላይ መሆን የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና ኅልውና ዋስትና ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህንን ሳይረዱ ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት በፖለቲካ ተከፋፍለዋል በሚል የተሳሳተ ስሌት ስህተት እንዳይፈጽሙ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደምም በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በፖለቲካ እሳቤ የሚለያዩ ሰዎች እንደነበሯት ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩነቶቻቸው ግን ለኢትዮጵያ ከመዋደቅ አላገዳቸውም።

በኢትዮጵያዊነት በመሰባሰብ ነጻ ሀገር እንዳስረከቡ ሁሉ ዛሬም ከተለያዩ ክልሎች፣ ብሔሮች ሃይማኖቶች እና የፖለቲካ እሳቤዎች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን ጠላት የኢትዮጵያን ኅልውና ለመንካት ሲፈልጉ በጋራ የምንቆምና ኅልውናችንን የምናስከብር መሆናችንን ጠላቶች ትምህርት ወስደው ደጋግመው እንዲያስቡበት በመጥቀስ አሳስበዋል።

ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በነበረው አውደ ውጊያ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይሎችና፣ ልዩ ልዩ መጠሪያ ያላቸውና የተለያዩ ዩኒፎርሞችን የለበሱ ኃይሎች በአንድነት ጠላትን ማሳፈርና ነጻነታችንን ማስቀጠል ችለዋልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እንደኢፕድ ዘገባ በዛሬው እለት የተሰጠው ሽልማት የህይወት እና የደም ዋጋ ለከፈሉ እንዲሁም በገንዘብና በእውቀት ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱት መላ ኢትዮጵያዊያን የተሰጠም ነው ብለዋል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!