ህወሓት እና ሸኔን የሚያወግዝ ሰልፍ በሐዋሳ እየተካሄደ ነው

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) -በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት የሚገልፅና  አሸባሪዎቹን ህወሓት እና ሸኔን የሚያወግዝ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

ሰልፉን እያካሄዱ የሚገኙት በሀዋሳና አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሲሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ማህበራዊ አደረጃጀቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ሰልፈኞቹ ሀገርን ለማዳን በሚደረገው ዘመቻ በግንባር እየተዋደቀ ላለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ቁርጠኝነት የተሞላበት አጋርነት የሚገልፁበት እንዲሁም አሸባሪው ህወሀት ሀገርን ለማፍረስ እየፈፀመ ያለውን እኩይ ተግባር የሚያወግዙ መልዕክቶችን በሀዋሳ ጎዳናዎች ላይ እያሰሙ ይገኛሉ።

የሰልፉ መዳረሻ በሆነው የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስቴድየም በተለይ በሲዳማ ባህላዊ ጭፈራ “ቄጣላ”ና ጣዕመ ዜማ የታጀቡ አንድነትን፣ የሀገርን ክብርና ሉአላዊነትን እንዲሁም ጀግንነትና መስዋዕትነትን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው፡፡

በዚህ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ በርካቶች ታድመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።