ህወሓት ንጹሐን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

ነሐሴ 13/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ላይ ወረራ እያካሄደ የሚገኘው የህወሓት ሽብር ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን በከፈተው ውጊያ ከሀገር መከላከያ፣ አማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ መቋቋም ሲያቅተው በተስፋ መቁረጥ ዛሬ ወደ ደብረታቦር ከተማ አራት ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ጥቃት መፈጸሙን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ከንቲባ ወንዴ መሰረት ገልጸዋል።

በጥቃቱም በቤት ውስጥ የነበሩ 5 ሰዎች ላይ የሞት፣ በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰና ግምቱ ያልታወቀ የግለሰቦች ቤትም መውደሙን ተቀዳሚ ከንቲባው ተናግረዋል።

አንድ ሕጻንን ጨምሮ በጥቃቱ የተገደሉት 3 ሴቶችና 2 ወንዶች የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ንጹሐንን ዒላማ አድርጎ ጥቃት እየፈፀመ የሚገኘውን አሸባሪው ህወሓትን እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረታቦር ከተማ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ያሉት አቶ ወንዴ ኅብረተሰቡ ሰርጎ ገቦች ወደ ከተማው እንዳይገቡ አካባቢውን በመጠበቅ እያደረገው ያለውን አኩሪ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በማይካድራ፣ ጋሊኮማ እና አጋምሳ ዜጎችን መጨፍጨፉም የሚታወስ ነው።