ህወሓት የአፋር ነፃ አውጪን በመጠቀም ወደ ጂቡቲ ለመሻገር የወጠነው እቅድ ከሽፏል- አቶ አወል አርባ

ሕግን በማስከበር ዘመቻ ወቅት መከላከያ እና የአፋር ክልል በመቀናጀት ባደረጉት ስምሪት በጁንታው ላይ ድልን መቀዳጀት መቻላቸውን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል ዐርባ ገለፁ፡፡

ሕወሓት ለጥፋት ዓላማው ማስፈፀሚያ ከአንድ ዓመት በላይ ሲያሰለጥንና ሲያስታጥቀው የነበረውንና ራሱን የአፋር ነፃ አውጪ ብሎ የሚጠራውን ኡጉጉሙ፤ ወደ ሠላም ፣ ድርድርና ልማት ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ጁንታው ኡጉጉሙን በመጠቀም ወደ ጂቡቲ ለመሻገር የወጠነው እቅድ ሊከሽፍበት ችሏል ብለዋል፡፡

የመከላከያ መረጃና የአፋር ክልል ይህንን ሴራ አስቀድመው በመረዳት በፍጥነት አካባቢውን ባይቆጣጠሩት ኑሮ ፣ ኡጉጉሙን በመጠቀም የጁንታው አመራሮች በቀላሉ ወደ ጅቡቲ ማምለጥ ይችሉ እንደነበር ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ መረጃ ከትህነግ ጎን ተሰልፈው የነበሩ 120 የአፋር ነፃ አውጪ ታጣቂዎች ሀገርን እንዲያፈርሱ በጥፋት ሀይሉ የታቀደላቸውን ጥፋት ተግባራዊ ሳያደርጉ ወደ አፋር ክልል በሰላም እንዲገቡ መደረጉን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።

ለውጡን ተከትሎ ከኤርትራ በርሀ ወደ ሀገር የገቡት “የኡጉጉሙ” ታጣቂዎች ለአንድ ዓመት ያህል በትህነግ ስልጠና ተሰጥቷቸው ለጥፋት ቢዘጋጁም በመከላከያ እና በአፋር ክልል መንግስት የጋራ ጥረት እንዲመለሱ ተደርገው የሰላም ውይይት መጀመራቸው ታውቋል።

ታጣቂዎቹ ሲገቡ የተቀበላቸው፣ ያኔ ለመሰደዳቸው ምክንያት የነበረው ትህነግ እድሉን በመጠቀም ለሌላ ጥፋት እንዳሰማራቸው ከሀገር መከላያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያሳያል።