በሳውዲ አረቢያው ባለሀብት ሼህ ሀምዛ የተመራ የልኡካን ቡድን ጅግጅጋ ገባ

በሳውዲ አረቢያው ባለሀብት ሼህ ሀምዛ የተመራ የልኡካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት  ጅግጅጋ ከተማ ገብቷል።

የሶማሌ ክልል የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሀሰን መሀመድ እና የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በገራድ ዊል ዋል አየር ማረፊያ በመገኘት ለባለሀብቶቹ አቀባበል አድርገዋል።

ባለሀብቶቹ ከ 5,000 እስከ 10,000 ቤቶች ፣ በፀሀይ የሚሰራ የሶላር መገጣጠሚያና የመኪና መገጣጠሚያ ድርጅት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ክልሉ እንደመጡ ተገልጿል።

የነዳጅ ካምፓኒ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሳውዲ አረቢያዊው ሼህ ሀምዛ አብዲአዚዝ አል ሱኬሪያና የጊፍት በሪል እስቴ ዋና ስራ  አስፈጻሚ አቶ ገብረእየሱስ ከክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ኡመር ጋር  በክልሉ ኢንቨስትመንት ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡

ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ሉኡካን ቡድኑ በክልሉ ለሚያከናውናቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች የክልሉ ህዝብና መንግስት ከጎናቸው እነደሚቆምም አረጋግጠዋል።

በክልሉ በሪል እስቴት መስክ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የባለ ሀብቶቹ ድርሻ የጎላ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የመገጣጠሚያ ካምፓኒዎቹ መገንባትም በኢኮኖሚው ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ባለሀብቶቹ በደገሀሌ ተገኝተው የግብርና ልማቶችንና ካሁን በፊት በስጋ ኤክስፖርት ዘርፍ ይሰራ የነበረውን የጄሽ ካምፓኒ መጎብኘታቸውን ከሶማሌ ክልል ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።