ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከበር በተለመደ ጨዋነት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

ግንቦት 04 / 2013 (ዋልታ) – ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከበር በተለመደ ጨዋነት ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ትላንት የተደረገውን የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃግብር በሰላም መከበርና በነገው ዕለት ለሚከበረው ለ1442ኛው አመተ ሂጅራ የኢድ አልፈጥር በዓል አከባባር ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ሱልጣን አማን ኤባ እንዳስታወቁት በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ የተደረገው የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃግብር አንድነታችንን ያጠናከረ፣ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ኢትዮጵያዊ እሴታችንን በግልጽ የታየበት ነው ብለዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ 1442ኛውን አመተ ሂጅራ የኢድ አልፈጥር በዓል ሲያክብርም የሃገርን አንድነት በመጠበቅ፣ የተቸገሩ ወገኖችን ከመርዳት ባለፈ ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መንገድ ሊያከብር እንደሚገባ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሀጂ ሱልጣን አማን ኤባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ባዩ ሽጉጤ በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር በትላንትናው ዕለት በኢፍጣር ፕሮግራም ላይ ያሳየውን ጨዋነትና አንድነት በመድገም ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሚደረገው የአከባበር ስነስርአት ካለምንም የጸጥታ ችግር ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ሃላፊው መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡