ህዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ ቀረበ

ጥቅምት 18/2014 (ዋልታ) በአሽባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የተጀመረው የህልውና ዘመቻ በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ መላው ህዝብ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ ትግሉን ሊያጠናክር እንደሚገባ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
በወጣቱና በፀጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ጥረት ከ800 የሚበልጡ ፀጉረ ልውጥ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ አሸባሪ ቡድኑ በክልሉ ህዝብም ሆነ በሀገሪቱ የደቀነው አደጋ ከባድ ነው ብለዋል።
“ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ ንፁሃንን ገድሏል፣ የግለሰቦችን ንብረት ዘርፏል፣ የተዘራ ሰብል አቃጥሏል ” ብለዋል።
የህዝብ መገልገያ የሆኑ ማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ዝርፊያና ማውደም ወንጀሎችን መፈፀሙን ጠቅሰው፤ የቡድኑን እኩይ ተግባር ሙሉ በሙሉ ለማስቆም የክተት ጥሪ ታውጆ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ለዚህ የህልውና ዘመቻም ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ የልዩ ሃይል፣ የሚሊሻና የፋኖ አባላት በተጨማሪ ወጣቱ በግንባር በመፋለምና ለፀጥታ ሃይሉ ደጀን በመሆን ታሪክ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።