ለህግ የበላይነት መከበር ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በአንድ ወገን ፍላጎትና ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ሰላም ሚኒስቴር ከደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በለውጥ ሂደቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትና የዜግነት ክብር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

የሰላም ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሰይድ እንደገለጹት፣ የፓናል ውይይቱ ዓላማ በፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚዎች መካከል ውይይትና ክርክር በማካሄድ በለውጡ ሂደት በሕግ የበላይነትና በዜግነት ክብር እሳቤዎች ላይ ግንዛቤና የሃሳብ ልዕልና ማዳበር ነው።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በሰላም ሚኒስቴር የዴሞክራሲና የዜግነት ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ሞገስ ደምሴ አገራዊ ለውጥና የህግ የበላይነት አቅጣጫዎች ላይ ያላቸውን ምልከታ አብራርተዋል።

የህግ የበላይነት ከቃል ወደ ህገ መንግስታዊነት እንዲሁም በህግ ከመግዛት ወደ በህግ ማስተዳደር መምጣቱንም ገልጸዋል።

የጸረ-ሽብር ህጉ መለወጡን እና የሲቪል ማህበራት ህግ መሻሻል ማሳያ መሆኑን አንስተው፣ የህግ ማስከበር ጉዳይ የገዢዎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ወደ ዜጋ ተኮር ደህንነት መጥቷል ብለዋል።

ሆኖም አሁን ላይ እየተስተዋሉ ያሉትን ውስንነቶች በመፍታት የለውጥ ፍላጎትን የሚመጥን የተቋማት አደረጃጀት በመዘርጋት የህግ የበላይነትን እውን ማድርግ ይቻላል ነው ያሉት።

በህግ የበላይነት ስም የሚወሰዱ እርምጃዎች መሠረታዊ የዜጎች መብቶችን የማይሸራርፉና የህዝብ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ መሆን እንደሚበቅባቸው በማንሳት የህግ የበላይነት በአንድ ወገን ፍላጎትና ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክና ሶሻል ዲቨሎፕመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ኮማንደር ደምመላሽ ካሳዬ የህግ የበላይነትና ፖሊሳዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ በሚል የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በማብራሪያቸውም የህግ የበላይነት ለአንድ ወገን የሚተው ባለመሆኑ ህዝብ ላይ ተከታታይ የግንዛቤ ስራ በመስራት እና በህግ የሚመራ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢዜአ ዘገባ እንዳመለከተው የፌዴራል መንግስት አመራሮች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ አካላት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በውይይቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ።