ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ18 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

መጋቢት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ18 ቢሊየን 973 ሚሊዮን 822 ሺሕ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ።

ገቢው ግንባታው ከተጀመረ 13 ዓመታት ሊሞላ ቀናት ለቀረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰብሰቡንም ነው የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ያስታወቀው፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ኅብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለና እስካሁን በነበረው ሂደት ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ሲሳተፍ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከሐምሌ እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ባሉት ሰባት ወራት 743 ሚሊየን 487 ሺሕ 159 ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም በቦንድ ግዢና በስጦታ እንዲሁም በ8100 A አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተሰበሰበ ገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

የግድቡ ግንባታ በሚቀጥሉት 7 ወራት እንደሚጠናቀቅ ከፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎች መገለጹን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የዘንድሮ 13ኛው ዓመት በሕብረት ችለናል በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርኃግብሮች እንደሚከበር ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም በኢትዮጵያዊያን የጋራ አንድነት የተገነባ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን አመላክተው ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና ያደገች ሀገር ለማስተላለፍ ታልሞ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ አፈፃፀሙ 95 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው