ለመከላከያ ሰራዊት የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ

መስከረም 6/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስር የሚተዳደሩ የተሃድሶ ልማት ማዕከላት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ500 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡

በዚህም የቀድሞ የጦር ጉዳተኞችና የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል 289 ሺህ 741 ብር፣ የአረጋዊያን ተሃድሶ ልማት ማዕከል 148 ሺህ 303 ብር፣ የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያ ልማት ማዕከል 115 ሺህ 412 ብር ድጋፋቸውን በዛሬው ዕለት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በማዕከሉ እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚገኙት እነዚህ ወገኖች ከሁለት ወር የምግብ ፍጆታቸው በመቀነስ ነው ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን መሆናቸውን ያረጋገጡት፡፡

ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረጉት የማዕከላቱ ተወካዮች የደም ልገሳ መርኃግብርም አከናውነዋል፡፡

በስነሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ኢትዮጵያ ወሰኗና ዳር ድንበሯ ተከብሮ የኖረችው በጀግኖቿ ኃያልነት ነው ብለዋል፡፡

ድጋፋን ላደረጉ የቀድሞ ጦር አባላትም ከዚህ ቀደም ከከፈላችሁት መስዋዕትነት ባሻገር ዛሬም አለን ብላችኃል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ