ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

ጥር 3/2014 (ዋልታ) ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት መርኃ ግብር የፊታችን እሁድ ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድነት ፓርክ የዳግማዊ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ ይካሄዳል።
የእራት ግብዣውን የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ፣ ጌት ፋክትና ሌሎች የዲያስፖራ ተቋማት ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
በ”አይዞን ኢትዮጵያ” የኦንላይን የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ክፍያ በመፈጸም በመርኃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝና በመርኃ ግብሩ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ዲያስፖራዎችም በመተግበሪያው በተለያየ ደረጃ የተዘጋጁትን ትኬቶች በመግዛት እንዲሁም በእራት ግብዣው ላይ በመሳተፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲደግፉ ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል።