በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በ#NoMore ንቅናቄ ያሳዩት አጋርነት ፓንአፍሪካኒዝም በድጋሚ እንድያንሰራራ ያደረገ ነው ተባለ

ጥር 3/3014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር በፓንአፍሪካኒዝም ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሀመድ እንድሪስ (ዶ/ር) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በበቃ #NoMore ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ያሳዩት አጋርነት ፓንአፍሪካኒዝም በድጋሚ እንድያንሰራራ እንዳደረገ ገልጸዋል።

የዲያስፖራ ኤጀንሲ በፓንአፍሪካኒዝም ስሜት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው አፍሪካዊያን በነጻነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ያሳዩት አጋርነት የፓንአፍሪካኒዝም ስሜትን ያሳየ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የአፍሪካ ፖለቲካ ከተጽዕኖ መውጣት ያልቻለው በድህነት ምክንያት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አፍሪካዊያን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል።

አፍሪካዊያን በፓንአፍሪካኒዝም ስሜት የሚፈልጉትን ማሳካት በሚችሉበት መንገድ ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

በመስከረም ቸርነት