ለአሸባሪው ሸኔ ሊተላለፉ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የሸኔ ቡደን እንዲደርሱ ታቅደው በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ሁለት ብሬን የተሰኙ የቡድን የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኢፕድ ከኦሮሚያ ፖሊስ ያገኘው መረጃ እንዳመለከተው መነሻቸውን አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ያደረጉ ሁለት ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3 ኦ.ሮ 78699 በሆነ ተሽከርካሪ ሁለት ብሬን የቡድን የጦር መሣሪያ በመጫን ለሸኔ የሽብር ቡድን ለማቀበል ሙከራ አድርገዋል።

ግለሰቦቹ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተደረገው ክትትል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሆለታ ከተማ በኦሮሚያ ፖሊስ አማካኝነት ከነጦር መሣሪያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ወደ ሕግ ቀርበው ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝ ተገልጿል።

መረጃው እንደጠቆመው ለሸኔ የሽብር ቡድንና ለሌሎችም ኢመደበኛ አደረጃጀቶች እንዲደርሱ ታቅደው ሲዘዋወሩ የነበሩ በርካታ የጦር መሣሪያዎች በጸጥታና በመረጃ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው።

ሕገ ወጦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ኅብረተሰቡ የሚሰጠው ጥቆማ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ሲሆን ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተገልጿል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW