መንግሥት ሰራዊቴን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የማስፈሩ መብት የእኔ ነው አለ

ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በማንኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰራዊቱን እንደሚያሰፍር መንግሥት ገለፀ፡፡
ይህን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሲሆኑ፤ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኢስያ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በማብራሪያቸው የሕወሓት አሸባሪ ኃይል በደረሰበት ምት ይዟቸው የነበሩ አብዛኛው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎችን በማስለቀቅ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የሽብር ቡድኑ ለሰላም ሲል በወረራ ከያዝኳቸው አካባቢዎች እንደለቀቀ አድርጎ የሚነዛው ወሬ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚቃረን ስለመሆኑም አንስተዋል።
መንግሥት ቡድኑ በሚሸሽባቸው እያንዳንዱ የትግራይ መንደሮች እግር በእግር በመከተታል የመግባት ፍላጎት የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን ቡድኑ መቸውንም ቢሆን መልሶ ጥቃት የማድረስ አቅሙ የተዳከመ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።