ለወደብ ቅርብ የሆኑ አካባቢዎችን በነጻ ንግድ ቀጠና በማካተት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ነው – ሰላማዊት ካሳ

መጋቢት 20/2015 (ዋልታ) ለወደብ ቅርብ የሆኑ አካባቢዎችን በነጻ ንግድ ቀጠና በማካተት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለፁ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህንን ያሉት የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን በጎበኙነት ወቅት ነው፡፡

በዚህም መንግስት ለምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ማሻሻል ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀው የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና መጀመሩ አንድ ማሳያ እንደሆነ በተለይ ለዋልታ ቲቪ ገልፀዋል፡፡

ይህ ደግሞ አገልግሎትን በአንድ ቦታ በማቅረብ የአለም አቀፍ አምራች ተቋማት ምርቶቻቸውን ከወደብ ወደ ማምረቻ በቀላሉ ለማድረስ እንዲያስችል ያግዛቸዋል ነው ያሉት ።

የነጻ ንግድ ቀጠና ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች በፖሊሲ የሚደገፉበትን አማራጭ በመስጠት መንግስት ለዘርፉ ቁርጠኛ አቋም አለውም ብለዋል።

የወጪ ንግዱን በማጠናከር፣ የሎጅስቲክስ ስርአቱ ያሉበትን ችግሮች በመፍታት ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትስስር ላይ በተግባር ላይ የተመሰረተ አካሄድን የምትከተል እንድትሆን የሚያስችል እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በሰላም ዲፕሎማ፣ በምጣኔ ሀብት ትስስር እንዲሁም የመሰረተ ልማት ትስስርን በማሻሻል የቀጠናውን ትብብር የማሻሻል ፍላጎት እንዳላት ተገልፆዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ኢንቨስት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት 1.2 ቢሊዮን አፍሪካዉያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ነው።

ሰለሞን በየነ