ለገና በዓል የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል- ኤጀንሲው

በመጪው ሳምንት ለሚከበረው የገና በዓል የግብርና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ተዋጽዖ እና ሌሎች የፍጆታ እቃዎችን ለሸማቹ ማህበረሰብ በህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ከገና በዓል ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ  ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ስራውን መጠናቀቁን  የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብነህ እምሩ አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከሚገኙ አምራች ዩኒየኖች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ከ19 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ ፣ 4 ሺህ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት፣ ከ180 የበላይ የእርድ በሬዎች፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ እንቁላል እንዲሁም ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እና ከ3500 ኪሎ ግራም በላይ የቅቤና አይብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ስራውን መጠናቀቁን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብነህ እምሩ ተናግረዋል፡፡

በአስራአንዱም ክፍለከተሞች የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በጉለሌ፣ በአራት ኪሎ፣ በአየር ጤና፣ በኮልፌ አካባቢ እና በ18 ማዞርያ አካባቢ ለዶሮ እና እንቅላል የመሸጫ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ ውብነህ ገልጸዋል፡፡

በበዓል ግብይት ወቅት ሸማቹ ማህበረሰብም እራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽን እየጠበቀ እንዲገበያይ ዋና ዳይሬክተሩ ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።