በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል 17ቱ በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር ዋሉ

በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል 17ቱ በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀረ ሽምቅና ልዩ ጥበቃ አድማ ብተና መምሪያ አስታወቀ።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ በኋላ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለእኩይ አላማ የተሰለፉ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድሉ፤ ሲያፈናቀሉና ንብረት ሲዘርፉ ቆይተዋል።

ለጥቃቱ በክልሉ ከህወሃት የጥፋት ቡድን ጋር የተመሳጠሩ አመራሮች ሚና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መኖሩም ታውቋል።

ከሰሞኑ በመተከል ዞን ቡለንና በቆጂ ወረዳዎች በዜጎች ላይ በተፈፀመው አሰቃቂ ግድያም የእነዚሁ አካላት የተቀነባበረ ሴራ መሆኑ ተደርሶበታል።

በአካባቢው ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመ የተቀናጀ ግብረ ሃይል የጸጥታና ህግ የማስከበር ስራውን ተረክቦ የተጠናከረ እርምጃውን ቀጥሏል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጸረ ሽምቅና ልዩ ጥበቃ አድማ ብተና መምሪያም ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ጋር በመቀናጀት ወንጀለኞችን በማደን ላይ ይገኛል።

የመምሪያው ዋና አዛዥ ኮማንደር ዶሳ ጎሹ ለኢዜአ እንዳሉት ክልሉ ከግብረ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት የታጠቁ ሃይሎችንና በግድያው እጃቸው ያለበትን ወንጀለኞች በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር እያዋልን ነው ብለዋል።

በህግ ማስከበሩ በርካታ ሽፍቶች እጅ እየሰጡና በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ግብረ ሃይሉ ባደረገው ዘመቻ ከዳንጉር፣ ድባጤ፣ ቡለንና ማንዱራ ወረዳዎች ጥቃት ካደረሱት ታጣቂዎች መካከል በአካባቢው ህዝብ ጥቆማና ትብብር 17 በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።

ከታጣቂዎቹ ጋር ከ29 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የባለ 5፣ 10፣ 50፣ 100 የሞባይል ካርዶች፣ 290 ቀስቶች፣ መድሃኒቶችና ሌሎች ቁሳቁሶችም ተይዘዋል።

ታጣቂ ቡድኑ የአማራ ልዩ ሃይልን ጨምሮ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ሃይልን ዩኒፎርም በመልበስ ነው ጥቃቱን የፈፀመው ያሉት ኮማንደር ዶሳ በህግ ማስከበሩ ታጣቂዎችን የማደን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ታጣቂዎች መካከል የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤትና የፖሊስ ዩኒፎርም ይዘው ተገኝተዋል።