ለ30ሺህ ዜጎች ነጻ የአይን ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

መጋቢት 10/2015 (ዋልታ) አልባሰር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ከያሲን ፈውንዴሽን ጋር በመተባበር ከየካቲት 23 እስከ መጋቢት 12/2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ለ30ሺህ ዜጎች ነጻ የአይን ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

የጤና የሚኒስትር አማካሪ ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል እንደተናገሩት አልባሳርና ያሲን ፋውንዴሽን ለ 23 አመታት ከ 500 ሺህ በላይ የአይን ህክምናን በማከምና ፣ ከ 50 ሺህ የሞራ ግርዶሽ በቀዶ ህክምና እንዲስተካከል እንዲሁም የአይነስውርነትን ከመከለከል አኳያ ላደረገው በጎ አድራጎት አመስግነዋል።

በዝግጅቱ ላይ የሳውዲ አረቢያ፣ የፓኪስታን አምባሳደሮች እንዲሁም አልባሳርና ያሲን ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጆች የተገኙ ሲሆን ከጤና ሚኒስቴር ጋር አብረው በአይን ህክምናና በሌሎች የጤና አገልግሎቶች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በአለርት ሆስፒታል በሁለት ቀናት ከ6ሺህ በላይ የአይን ህክምና ፣ ለ250 የሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና እና ለ1ሺህ ታካሚዎች የመነፅር ድጋፍ ማግኘታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በአለርት ሆስፒታል የነጻ ህክምና አገልግሎቱ መክፈቻ ስነ-ስርዓቱ የተካሄደ ሲሆን አገልግሎቱ በወራቤ ኮምፕሬሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጅማ ዩኒቨርሰቲ ሆስፒታልና በአዲስ አበባ አለርት ኮምፕሬሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ ይገኛል።