ሊንክዲንም እንደ ቲክቶክ…

ሰዎች ሥራና ተያያዥ ሙያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎቸን ሲፈልጉ የመጀመርያ ምርጫቸው የሚያደርጉት ሊንክዲን የተሰኘውን የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው፡፡ በዚህም ይህ የማኅበራዊ የትስስር ገጽ አይነት በእድሜ ተለቅ ያሉ ተጠቃሚዎች እንደሚበዙ ይታመናል፡፡

ታዲያ ይኸን ያስተዋለው ሊንክዲን በእድሜ ወጣት እና ታዳጊ የሆኑ ተጠቃሚዎችን ለማፍራት በሚል በሞባይል መተግበሪያው ላይ ልክ እንደቲክቶክ አጫጭር ቪዲዮዎቸን መጫንና እያሣለፉ (scroll) እያደረጉ መመልከት የሚያስቸል አዲስ አሰራርን ጨምሯል፡፡

በዚሁ ዙሪያ አስተያየቷን የሰጠችው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማካሪ ሪሃ ፍሪማን ሊንክዲን የተጠቃሚዎቹን ቁጥር የሚጨምርለት ከሆነ ጥሩ መሆኑን አንስታ ነገር ግን ማኅበራዊ ገጾች የራሳቸውን መለያ ይዘው ቢቀጥሉ የተሻለ መሆኑን ትናገራለች፡፡

አማካሪዋ አክላም ሰዎች እየዘፈኑ ቪዲዮ ሲሰሩ ማየት የሚያዝናና ነገር ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ሊንክዲን ላይ ማየት አልመርጥም ብላለች፡፡

የቲክቶክ ቪዲዮዎች ዝነኝነትን ተከትሎ ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች መሰል የቪዲዮ መመልከቻ አሰራር መተግበር ጀምረዋል፡፡ ለአብነትም የማርክ ዙከርበርግ የሆኑት ፌስቡክና ኢንስታግራም “ሪል” በሚል መጠሪያ መሰል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ዩቲዩብም እንደዚሁ የ60 ሰከንድ ቪዲዮዎች ማስተላለፍ የሚቻልበት” ዩትዩብ ሾርት” የተሰኘ አሰራር መጨመሩ የሚታወስ ሲሆን የቀድሞ ትዊተር የአሁኑ ኤክስም ይህን አይነት አሰራር ጀምሯል፡፡

የሊንክዲን የስልክ መተግበርያም ይህንን መሰል አሰራር በስልክ መተግበርያው ላይ ሲያስጀምር ተቀባይነት ያገኝ ይሆን የሚለው የብዙዎችን ጥያቄ መሆኑን ኦን ላይን ሜል ዘግቧል፡፡