ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ኩራት፣ የይቻላል ተምሳሌት!

ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ…

መጋቢት 24 ቀን በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳክቶ ከመገባደጃው ጫፍ ደርሷል። ግድቡ ከዚህ ስኬት ሲደርስ እልፍ አእላፍ ችግሮችንና የሴራ ወጥመዶችን አልፎ ነው።

የግድቡ መሠረት የተጀመረበት 13ኛ ዓመቱ “በኅብረት ችለናል!” በሚል መሪ መልእክት የሚከበረዉ ከጅምሩ እስከዛሬ ሕዝባችን ላደረገዉ ያልተቋረጠ ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና ለማቅረብ ነው፡፡

ግድቡን ለመገንባት ስናቅድና ስንጀምር ጫጫታና ጫናዉ ቀላል አልነበረም። የኢትዮጵያውያን ሕልምና ተስፋ ከጅምሩ እንዲጨናገፍ አንዳንድ ሀገራት በጋራ አድመው አሲረውብናል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድንገለልና እንድንነጠል ከፍተኛ ዘመቻ ተከፍቶብናል። ባልፈረምነው የቅኝ ገዥዎች ውል ሊያስገድዱንና ውጥኑ ከመነሻዉ እንዲጨናገፍ ሞክረዋል፡፡አንዳንዶቹም “ይጀምሩታል እንጂ አይጨርሱትም!” እያሉ የብድር አማራጮችን ሁሉ ሲያመክኑብን ቆይተዋል፡፡

ሁሉን አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁመን ግድቡን ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ ስንሸጋገርም ዘመቻውን ዳግም በመክፈትና ኃይል በማስተባበር የፀጥታዉ ምክር ቤት ልማትን እንደጦርነት እንዲመክርበት ተደርጓል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በጋራ የጀመርነዉና አስፈላጊዉን መሥዋዕትነት ሁሉ የምንከፍልለት የኩራታችንና አንድነታችን መገለጫ ፕሮጀክት ነበርና ከዚህ አድርሰነዋል፡፡

ግድቡን የምንገድበው ማንንም ለመጉዳት አይደለም፣ መነሻችን ሕዝባችንን ከጨለማ ኑሮ ለማላቀቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሻታችን ደግሞ የሚጎዳም፣ የተጎዳም አካል የለም፣ አይኖርምም፡፡ በራሳችን ወንዝና በራሳችን ሀገር፣ በራሳችን አቅም እንዳንለማ ሲፍጨረጨሩ የነበሩ ሁሉ ብድር ለማስከልከል፣ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዳያደርጉ ለመወትወትና ልዩ ልዩ ማሰናከያዎችን ለመደርደር በእጅጉ ደክመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን የተንኮል መረቦችን በጋራ እየበጣጠሱ፣ ተማሪዎች ከዕለት ጉርሳቸዉ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ ነጋዴዎች ከወረታቸው፣ ጡሮተኞች ከአነስተኛ አበላቸው፣ የጉልበት ሠራተኞች ከዕለት ምንዳቸዉ፣ የፀጥታ ኃይሎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሬሽናቸው፣ በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን ከአነስተኛ ገቢያቸዉ፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በላባቸው ካፈሩት ፍሬ እየቀነሱ ግድቡን ከማጠናቀቂያ ምዕራፉ አድርሰውታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ አስተዋጽኦ ያደረጉት ገንዘባቸዉን ብቻ አልነበረም፤ ደስታቸዉን፣ ኀዘናቸዉን ሁሉ ጭምር እንጂ፡፡ የሠርጋቸዉን ወጪ ቀንሰው ሙሽሮች ለግድቡ ሰጥተዋል፤ የሟች ቤተሰቦቻቸዉን የሙት ዓመት መታሰቢያ ለሕዳሴ ግድብ አበርክተዋል፡፡ በአጠቃላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ልክ እንደ ዓድዋ ድል መላዉ ኢትዮጵያውያን የተረባረቡበት የወል ድል ነው፤ በጋራ ጀምረን የማንጨርሰው ጉዳይ እንደሌለ ማሳያም ነው፡፡

የኃይል አቅርቦት ዓለማቀፍ ችግር ነው፤ በተለይ ደግሞ ታዳሽ ኃይል ማመንጨት ዓለማቀፍ ድጋፍ የሚያስገኝ ተግባር ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን በራሳችን ወንዝ፣ በራሳችን ዐቅም፣ በራሳችን ሀገር ታዳሽ ኃይል እንዳናመነጭ በርካቶች ተረባረቡብን፡፡ ነገር ግን ሊያዘገዩን እንጅ ከሕልማችን መዳረሻ ሊያስቆሙን አልቻሉም፤ ምክንያቱም በጋራ ቆመናልና፡፡

አሁን ላይ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ፕሮጀክቶችን በራስ ዐቅም ጀምሮ የመጨረስ ዐቅም እንዳለን አሳይተናል፡፡ አጠቃላይ ሥራዉ በመጠናቀቅ ላይ የደረሰው ግድባችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፤ ለቀሪ ሥራዎቹም ኢትዮጵያውያን የመጨረሻዎቹን ሴኮንዶች ማርሽ ቀይረዉ ጭምር ማስደመም ይችላሉና፡፡ ከ18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አዋጥተው ግድቡን በማገባደጃ ምዕራፍ ላይ ያደረሱ ኢትዮያውያን ለቀሪዉ የማንንም ድጋፍ አይጠብቁምና፡፡

መንግሥት ዘንድሮ የግድቡን ግንባታ የጅማሮ 13ኛ ዓመት ሲያከብር እንደከዚህ ቀደሙ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እየጠየቀ ብቻ አይደለም፤ በጋራ ተሳትፎ ከዚህ ስላደረሱት እያመሰገነ እንጂ፡፡ እንደ ሕዳሴ ግድብ ሕዝብ በነቂስ የተሳተፈበት ፕሮጀክት በዓለም ስለመኖሩ እንጠራጠራለን፤ እንደ ሕዳሴ ግድብ በዓለማቀፍ መድረክ እየተፈተነ ከዚህ ደረጃ የደረሰ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ግድብም እምብዛም አይታወቅም፡፡ ሆኖም ግን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የተሳካዉ በመላዉ ኢትዮጵያውያን የእንችላለን መንፈስና የጋራ ጥረት ነው፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችንም የኢትዮጵያን ሁሉ የጋራ ድልና የይቻላል መንፈስ ተምሳሌት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

በኢትዮጵያውያን ኅብረት ግድቡ ይጠናቀቃል፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናችን ይረጋገጣል!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት