ኢትዮጵያ ለሳዑዲ-አፍሪካ ግንኙነት ድልድይ አገር ነች – የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር

መጋቢት 23/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ለሳዑዲ – አፍሪካ ግንኙነት ድልድይ እና ወሳኝ አገር ነች ሲሉ የሳዑዲ አረቢያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን ገለጹ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተው ልዑክ በሳዑዲ አረቢያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሳዑዲ ዓረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን የላኩትን መልዕክት ለሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስረክበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በጸጥታ እና በሰው ሃይል ሥምሪት ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ የጋራ ኮሚሽን ሥብሰባ ማካሄድ፣ በሂደት ላይ ያለውን የሰለጠነ የሞያተኛ የሥራ ሥምሪት ስምምነት መፈራረም እና በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሕጋዊ የባሕር በር ጥያቄ በቀጣናው ለሚካሄደው የምጣኔ ሃብት ውህደት የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተም ገለጻ መደረጉ ተጠቅሷል።
የሳኡዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር እያስመዘገበችው ያለውን እድገት አድንቀዋል።

ሁለቱ ወገኖች በወቅታዊ የቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት ሃሰብ በመለዋወጥ በአካባቢው ሰላም እና ጸጥታ እንዲሰፍን በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።