ሌጲስ የኢኮቱሪዝም መንደር …

ሌጲስ የኢኮቱሪዝም መንደር

#ሀገሬ

ሌጲስ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ እና ቆሬ ወረዳዎች መካከል የሚገኝ ተመራጭ የኢኮቱሪዝም መንደር ነው።

ሌጲስ ከአርሲ ነገሌ ከተማ በስተምሥራቅ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ 140 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ያገኙታል።

የሌጲስ ኢኮቱሪዝም መንደር የዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት እውቅና ሽልማትን በወርሃ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ከተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አግኝቷል።

የቱሪዝም መንደሩ የኢኮ ቱሪዝም መስፈርቶችን በማሟላት ነበር ከመላው ዓለም ከተውጣጡ 260 መንደሮች ጋር በመፎካከር ምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደር ሆኖ የዕውቅና ሽልማት ማግኘት የቻለው።

ለመሆኑ ኢኮቱሪዝም ሲባል ምን ማለት ይሁን?

ኢኮቱሪዝም ተፈጥሮን በዘላቂነት በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰብ ባህልና ነባር እሴቶችን በማይበርዝ መልኩ እየጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት ሲሆን ተፈጥሮንና ልማትን በማመጣጠን ለማህበረሰቡ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ሌጲስን የኢኮቱሪዝም መንደር የዕውቅና ተሸላሚ ያደረጉትም የኢኮ ቱሪዝም መስፈርቶችን አሟልቶ መገኘቱ ነው።

ሌጲስ ዘለቄታ ያለው የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ የሚካሄድበት ሲሆን በጥብቅ ጫካ የሚገኙ ወንዞችና ፏፏቴዎች፣ የዱር አራዊቶች እንዲሁም ብዙ ዓይነት ዝርያ ያላቸው አዕዋፋትም መገለጫዎቹ ናቸው።

አስደናቂ ዕይታ ያላቸው ተራራና ሸለቆዎች፣ ለዘመናት በህብረተሰቡ ተጠብቆ የኖረው ዓመታዊ የፈረስ ጉግስ የሚካሄድበትና በጫካ የተከበበው ወንተሼ ሜዳ አንዱ የሌጲስ መንደር የቱሪስት መስህብ ነው።

ከአካባቢው ተፈጥሮ ጋር የተቀናጁና ተፈጥሮን ሳይጎዱ የሚዘጋጁ ባህላዊ የዕደ ጥበብ ስራዎች እንዲሁም ያልተበረዘ ባህልና የእንግዳ አቀባበል እሴቶችም የኢኮቱሪዝም መንደሩን ተመራጭ አድርጎታል።

በሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ የተለያዩ የዱር አራዊቶች የሚገኙ ሲሆን የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው አዕዋፋት፣ ከርከሮ፣ ኒያላ፣ ነብር፣ ጦጣዎች እና ጉሬዛዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

የቱሪዝም መንደሩ ውብ ተፈጥሮን የሚያስቃኝ መልከዓ ምድር ሰንሰለታማ ተራሮች እና ሸለቆዎችን አቅፎ የያዘ በመሆኑ የእግር ጉዞና ተራራ መውጣት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ምርጥ መዳረሻም ነው ሌጲስ።

ይህ ውብ የኢኮቱሪዝም መንደር ሌጲስ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የተቀመጡትን ዘጠኝ የመምረጫ መስፈርቶች አሟልቶ ነበር በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደርነት ዕውቅናን ያገኘው።

ሌጲስ የቱሪዝም መንደር ወንጪና እና ጮቄ የኢኮቱሪዝም መንደሮችን ተከትሎ ምርጥ የቱሪዝም መንደርነት ዕውቅናን በማግኘት በሀገራችን የኢኮቱሪዝም መንደርን ሦስት አድርሶታል።

ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ የማድረግ ባህላዊ እሴቶቻችን በጠበቀ መልኩ የቱሪዝም መስሕቦችን የመለየት፣ የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች ከተሠሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የኢኮ ቱሪዝም መንደሮችን ማየት እንደሚቻል እነዚህ ዕውቅና ያገኙ ምርጥ የቱሪዝም መንደሮች ማሣያዎች ናቸው።

ተፈጥሮን እየተንከባከቡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በማስፋፋት እንዲሁም የጎቢኚዎችን ቆይታ በማራዘም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ለመሆን ደግሞ ከባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ምርጥ የቱሪዝም መንደሮችን ማወዳደርና ዕውቅና መስጠት የጀመረው እ.ኤ.አ ከ2021 ጀምሮ ነው።
ቸር እንሰንብት!

በሠራዊት ሸሎ