ለህዝቡ የገባነውን ቃል በተግባር እያረጋገጥን እንቀጥላለን – ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ

መጋቢት 16/2016 (አዲስ ዋልታ) በሶማሌ ክልል የህዝቡን መሰረተ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ገለጹ።

የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አባላት ላለፉት 15 ቀናት በየደረጃው ሲካሄድ የነበረው ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ በጅግጅጋ ተካሂዷል፡፡

በማጠቃለያ መድረኩ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ ዑመር ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በክልሉ የተከናወኑ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ የልማት ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የስራ እድል ፈጠራን ለአብነት ጠቅሰው በቱሪዝምና በአረንጓዴ አሻራ የተገኙ ስኬታማ ስራዎችም ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩልም በመንገድ ልማት በተለይም በዋርዴርና ሀርጌሌ የተጀመሩ የአስፋልት መንገዶች እንዲጠናቀቁ በማድረግ ለህዝቡ የገባነውን ቃል በተግባር እያረጋገጥን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ ኡመር የብልፅግና ጉዟችንን ለማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች መመለስ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ የፓርቲ ስነ ምግባር ተላብሰን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በየመድረኩ በየደረጃው በተካሄዱ ኮንፍረንሶች መግባባት ላይ የደረስንባቸውን ሃሳቦች በላቀ ቁርጠኝነት ለማስፈጸም ቃል የምንገባበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በመድረኩ ላይ የፓርቲው የሁለት ዓመት ተኩል የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የፓርቲው የስነ ምግባርና ክትትል ኮሚሽን ሪፖርት ቀርበው በሙሉ ድምፅ መጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።