“ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም!” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 1/2015 (ዋልታ) “ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያወጡት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም!”

የዓለማችን ታላላቅ የውትድርና ጠበብት እንደሚናገሩት ከሆነ፤ የአንድ ሀገር ሠራዊት ጥንካሬ የሚወሰነው በዋናነት በማዕከላዊነቱና በጠንካራ የዕዝ ሰንሰለቱ ነው። አሥር ቦታ ተበጣጥሶ ከተዋቀረ መቶ ሠራዊት ይልቅ በአንድ ማዕከል በሥርዓት የተደራጀ ሠላሳ ሠራዊት ይበልጥ ጠንካራ እንደሚሆን በውትድርና አካዳሚ ውስጥ ያለፉ ሰዎች በትክክል ይገነዘቡታል። በመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀት የቁጥር ብልጫ የሚጫወተው የራሱ ሚና እንዳለ ቢታመንም፤ ቁጥሩ በጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት፣ በጥብቅ ዲሲፕሊን፣ በተደራጀ ስትራቴጂ እንዲሁም በረቀቁ መሳሪያዎችና ሥልጠናዎች እስካልታገዘ ድረስ የሠራዊት አቅም አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። በተለይም በዘመናዊው ዓለም የሠራዊትን አቅም የሚለካው “ብዛት” ሳይሆን “ጥራት” እንደሆነ እሙን ነው። የሠራዊት ጥራት አንድም ከዶክትሪኑ፣ ከሥልጠናው፣ ከትጥቁና ከዕዝ ሰንሰለቱ የሚመነጭ ሲሆን፤ ወታደራዊ ማዕከላዊነት ለመከላከያ ሠራዊት “ጥራት” እጅግ ወሳኝ ነው።

ሀገራት አጣዳፊ የጸጥታና የደህንነት ሥጋቶች ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ፣ በማዕከላዊ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አማካኝነት የሚጋረጡባቸውን ሥጋቶች መመከት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ እንደ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ያሉ፣ ለማቋቋም እምብዛም አዳጋች የማይሆኑ አነስተኛና መካከለኛ የጸጥታ ኃይሎችን አደራጅተው ለመንቀሳቀስ ይገደዳሉ። እነዚህ ኃይሎች በጥድፊያ ውስጥ በጊዜያዊነት እንደመቋቋማቸው መጠን የሚሰጡትም ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ይታወቃል። በውትድርና ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም በጊዜያዊነት የሚቀመጡ መፍትሔዎችን ዘላቂ አድርጎ መውሰድ በራሱ አደጋ ሊጋርጥ እንደሚችል ታምኖበት ነው – ወደእነደዚህ ዓይነት የመፍትሔ አማራጮች የሚገባው። ትክክለኛ ጊዜው ሲደርስም፣ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙ የመፍትሔ አማራጮች ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ማድረግ የተለመደ አካሄድ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑ አያጠያይቅም።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስቀድሞ በሪፎርም፣ አሁን ደግሞ በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ውጊያዎች ጠንክሮና በቅቶ እየተገነባ ይገኛል። ይሄንን የመከላከያ ሠራዊት ማዕከላዊ በሆነ መልኩ ማጠናከርና ለሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲበቃ ማድረግ ተገቢና ወቅታዊነቱ አያጠያይቅም። ይሄን መሠረት በማድረግ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎች በተቻለ መጠን የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ እየተሠራ ይገኛል። ወደ መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል ያልፈለጉ ደግሞ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልሎች ፖሊስ እንዲገቡ ምርጫ ተቀምጦላቸዋል።

የየክልሉ ልዩ ኃይሎች ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ፈተና በገጠማት ጊዜ ሕይወታቸውን ሠውተዋል። በየአካባቢው የተሰጣቸው ግዳጆችን በመወጣት ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ታግለዋል። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የልዩ ኃይል አደረጃጀት አስፈላጊ አይደለም ማለት የልዩ ኃይል አባላት አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ለሀገራችን የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉ፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በዐቅማቸው የተወጡ፤ ለወደፊትም በተሻለና ይበልጥ ኢትዮጵያን ማገልገል በሚያስችላቸው ቦታዎች ላይ እንደ የፍላጎታቸው ተመድበው ያገለግላሉ።

የልዩ ኃይል አባላትን ወደ መከላከያ ወይም ወደ ፖሊስ እንዲገቡ የማድረግ አጀንዳ ለረጅም ጊዜ ሲታሰብበትና ሲመከርበት የቆየ ጉዳይ ነው። አጀንዳው በተለያዩ ጊዜያት በአመራርም በሕዝብ መድረኮችም ተነሥቶ ነበር። ጉዳዩ እንዲነሣ ያደረጉት ሁለት ምክንያቶች ናቸው። አንዱ የልዩ ኃይል አባላትን ጥቅማ ጥቅም፣ ዕድገትና ማዕረግ የተመለከተ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አደረጃጀቱን ምክንያት በማድረግ በተደጋጋሚ ያጋጠሙንን ፈተናዎች የተመለከተ ነው።

የልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በተገቢው መንገድ መስተናገድ እንዳለባቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። በሀገር ውስጥና በውጭ የሚሰጡ ወታደራዊ ትምህርቶችንና ሥልጠናዎች ሊደርሷቸው ያስፈልጋል። የላቁ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ሊታጠቁ ይገባል። ከፍ ያሉትን ወታደራዊ ማዕረጎች በቆይታቸውና በጀብዷቸው ሊቀዳጁ ይገባል። ይህ መሆን የሚችለው ደግሞ ወደ መደበኛ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ማለትም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ አልያም በፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ውስጥ እና በክልሎች ፖሊስ ሠራዊት ውስጥ መካተት ሲችሉ ብቻ ነው። እነዚህን የመሰሉ በውጊያ የተፈተኑ ኃይሎች በጊዜያዊ የልዩ ኃይል አደረጃጀት ብቻ ወስኖ ማስቀረት ሀገርንም አባላቱንም መጉዳት ነው።

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

ጊዜያዊ የመፍትሔ አማራጭን በዘላቂነት መወሰድ የሚጋርጠው አደጋ ይኖራል ስንል በተጨባጭ መሠረት ላይ ቆመን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ኢትዮጵያ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት የተገዳደሩ ፈተናዎች ገጥመዋት እንደነበር አይዘነጋም። ከአንድነትና ሉአላዊነት ሥጋትነት በመለስም በክልሎች መካከል የማያስፈልግ ተፎካካሪነትና ተገዳዳሪነት እንዲፈጠር መንስኤ ሲሆኑ እናያለን። ከሕገ ወጥ የኬላ ዝርጋታ፣ ከኮንትሮባንድ፣ ከሽፍትነት፣ ወዘተ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችም እየተስተዋሉ ናቸው። እነዚህ ችግሮች የመነጩት ለጊዜያዊ መፍትሄነት የፈጠርናቸውን አደረጃጀቶች እንደ ዘላቂ መፍትሄ መቁጠር በመጀመራችን ነው። በመሆኑም ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም ሲባል ነገሮችን በአግባቡ ፈትሾ አስፈላጊውን የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው።

የክልል ልዩ ኃይሎችን ጉዳይ በይደር ያቆየንበት ምክንያት ነበረን። አንደኛው የመከላከያ ኃይላችንን በበቂ መልኩ ለማደራጀት ጊዜና ዐቅም ስላስፈለገን ነበር። ሁለተኛው ደግሞ በወቅቱ በሀገራችን ላይ ከተጋረጠብን አደጋ አንጻር እነዚህን መሳይ ሥራዎች ለማከናወን የሚያስችል ሁኔታ ስላልተፈጠረ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታትም ከሕዝብ ጋር በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች ከሚነሡ ጉዳዮች አንዱ የልዩ ኃይሎች ጉዳይ ነበር። ካጋጠሙን ፈተናዎች በመነሣት ልዩ ኃይሎች ወደ መከላከያ እንዲጠቃለሉ ሕዝቡ ጠይቋል። የልዩ ኃይል አባላትም ከሜካናያዝድ ሥልጠና፣ ከደመወዝ፣ ከማዕረግ ዕድገት፣ ከትምህርት ዕድሎችና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነገሩን በተደጋጋሚ አንሥተውታል።

የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ ለማድረግ ሲወሰን፣ ተገቢው ዝግጅት ተደርጎበት ነው። በመርሕ ደረጃ የተቀመጠውም የሚከተለው ነው።

  • የልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት እንዲወያዩበት ማድረግ
  • ወደ ሌሎች ጸጥታ መዋቅሮች የማስገባቱ ተግባር በሁሉም የክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ እንዲተገበር
  • አባላቱ ሦስት አማራጮች እንዲሰጣቸው (ወደ መከላከያ፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል ፖሊስ እንዲገቡ)
  • ጉዳዩ የትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሳይሆን የበለጠ ሥልጠናና ትጥቅ አግኝተው ሀገርን በተሻለ ወደሚያገለግሉባቸው መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑን
  • ይሄንን ሥራ ለማደናቀፍ የሚነሡ አካላት እንደሚኖሩ፤ መጀመሪያ በመወያየትና በማሳመን፤ ከዚህ ያለፈ ተግባር የሚፈጽሙ ካሉም ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ የሚሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በብሔራዊ ደረጃ የተደራጀበትን ታሪክ ከተመለከትን የተለያዩ ወታደራዊ አደረጃጀቶችን ወደ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት በማዋሐድ የተከናወነ መሆኑን እናያለን። የሌሎች ሀገሮች ታሪክም ተመሳሳይ ነው። ከብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ውጭ የሆኑ አደረጃጀቶች በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ ሊፈጠሩ ይችላሉ። በዐማጽያን ትግል ምክንያት የሚፈጠርበት ጊዜ አለ። እነዚህ ዐማጽያን ወደ ሰላማዊ መንገድ ሲመለሱ ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ የታጠቁ አካላትን መርምሮና መልምሎ ወደ መከላከያ ሠራዊትነት መቀላቀል ነው። በ1983 ዓ.ም. መከናወን ነበረበት ብለን ለብዙ ዓመታት በተደጋጋሚ የኮነንነው አንዱ ጉዳይ ይሄ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ ሀገር ፈተና ላይ ስትወድቅ የሚፈጠሩ ወታደራዊ አደረጃጀቶችም ይኖራሉ። ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣልያን በተወረረችበት ጊዜ በታዋቂ ዐርበኞች ሥር የተፈጠሩ ወታደራዊ አደረጃጀቶች ለዚህ ምሳሌ ናቸው። ኢትዮጵያ ሀገራችን በፋሺስት ጣልያን በተወረረች ጊዜ የተለያዩ የዐርበኛ መሪዎች ጦር አደራጅተው በዱር በገደሉ ዘምተው ነበር። ጣልያን ድል ሆኖ ነጻነት ሲመለስ ከፊሎቹ ወደ መከላከያ ሠራዊት ሲገቡ፣ ሌሎች ወደ ሲቪል ሕይወት ተመልሰዋል።

ዛሬም የየክልሉ ልዩ ኃይሎችን እስከ ዛሬ ለሰጡት አገልግሎት አመስግነን፣ ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የምናካትትበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ይህ ውሳኔ በሁሉም ክልል አመራሮች በጋራ የተወሰነና በጋራ የሚተገበር ነው። አብዛኞቹ ክልሎችም ሠራዊት ለማስተዳደር የሚያስችል የኢኮኖሚ ዐቅም የላቸውም። ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በፌዴራል መንግሥት ከሚሰጣቸው በጀት ለልዩ ኃይላቸው የሚጠቀሙ ናቸው። የዚህ ወይም የዚያ ክልል ልዩ ኃይል ብቻውን ትጥቅ ሊፈታ ነው፤ የዚህኛው ክልል ይቆይ ተብሏል፤ ይሄን ወይም ያንን ሕዝብ ለመጉዳት የተደረገ ነው የሚሉ ውዥንብሮችን የሚነዙ አካላት ገሚሶቹ ባለማወቅ ሲሆን፤ የተቀሩት ዓላማቸው ሕዝብ ከማበጣበጥ የዘለለ አይደለም። ጥቂት የማይባሉትም የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ አለበት ብለው ሲጽፉና ሲሞግቱ የከረሙ ናቸው፤ ጠለቅ ብለን ብንፈትሻቸው፥ ይሁን ሲሏቸው አይሁን፣ አይሁን ሲሏቸው ይሁን የማለት ልማድ የተጠናወታቸው ሆነው እናገኛቸዋለን።

ከዚህ በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው ወንጀልን በመከላከልና አካባቢያዊ ጸጥታን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ከየትኛውም ኃይል የሚሰነዘር፣ የሀገርን ድንበር፣ ህልውናና ሉዓላዊነት የሚዳፈር ኃይል ሲነሣ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱ እርምጃ ይወስዳል። ለዚህ የሚሆን አደረጃጀትም በተግባር ላይ ውሏል። የክልሎች ፉክክርና ትብብር በልዩ ኃይል ግንባታ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ልማትና በዴሞክራሲያዊ ባህል ላይ ይሆናል። ይህ ውሳኔም ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል። ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳትና ለማሳመን ጥረት እናደርጋለን። ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ደግሞ ተገቢው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወሰዳል። ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል። በመሆኑም የሚመለከታቸው ተቋማትና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ፣ የውሳኔውን ሃገራዊ ፋይዳና የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት በማስገባት ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንድታደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዝያ፣ 2015 ዓ.ም