መንግሥት ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አስፈጻሚው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆኑን እና መንግሥት ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህንን የገለጹት ኢትዮጵያ ከሳምንታት በኋላ የምታካሂደው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ላሉት አምስቱ ሴናተሮች ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤያቸው ነው።
ሴናተሮቹ ከሳምንታት በኋላ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ማለታቸው ተገልጿል።
ሴናተሮቹ ይህን ያሉት በቅርቡ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለተሾሙት አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው።
አምባሳደር ፍጹም ለሴናተሮቹ በሰጡት ምላሽ፤ መጪው ሀገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ታሪካዊ ነው ካሉ በኋላ፣ ምርጫውን የሚያስፈጽመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ታሪክ ገለልተኛው ነው ብለዋል።
አክለውም መንግሥትም ምርጫው ነጻ እና ግልጽ እንዲሆን ያላሰለስ ጥረት አድርጓል እያደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ደብዳቤያቸው በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ 47 ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ8ሺህ በላይ እጩዎች መመዝገባቸውን አስታውሰው ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶችን የፍትሕ አካሉ በገለልተኛነት ይመለከታቸዋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም ምርጫውን እንዲታዘቡ ጥሪ እንደቀረበላቸውም ገልጸዋል።
በየትኛውም አገር የሚካሄድ ምርጫ ፍጹም ነው ተብሎ አይጠበቅም ያሉት አምባሳደር ፍጹም፤ 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ያሸጋግራታል ብለን እናምናለን ብለዋል።
አምባሳደሩ በደብዳቤያቸው ላይ ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ሴናተሮቹ ቤንጃሚን ኤል ካርዲን፣ ቲም ኬይን፣ ጃኪ ሮስን፣ ኮርይ ኤ ቡከር እና ኤድዋርድ ጄ ማርኬይ ስለመጪው አገራዊ ምርጫ፣ ስለትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ስፍራዎች ስላሉ ግጭቶች ለተሿሚው ልዩ መልዕክተኛ መልዕከታቸውን አጋርተው እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል።