የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የሚፈጠረውን ጫና ለመቋቋም አንድነትን ማጠናከር መፍትሄ ነው ተባለ

አምበሳደር ዲና ሙፍቲ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ላይ የሚፈጠረውን ዓለምአቀፍ ጫና ተቋቁሞ አሸናፍ ለመሆን ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ብቸኛ መፍትሄ ነው ተባለ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት “ጉሚ በለል” የተሰኘ ሳምንታዊ የውይይት መድረክ “ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሀገራዊ ክብራችን” በሚል ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምበሳደር ዲና ሙፍቲ አሁን ያለንበት ጊዜ ለኢትዮጵያ በታሪኳ ፈታኝ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በውስጣዊ አንድነቷ ተዳክማለች ብንገፋት ትወድቃለች በሚል የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገሪቱን በመበተን ጥቅማቸውን ለማስከበር እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ግብፅ እና ሱዳን የግድቡ ግንባታ እንደማይጎዳቸው ያውቃሉ ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ትልቁ የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ታድጋለች፤ ትበለፅጋለት፤ እኛን ትበልጠናለች የሚል ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የረዥም ዓመታት ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም በዋና ዋና ሀገራዊ ምሰሶ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ላይ አለመደረሱ በዲፕሎማሲው ስራ ላይ ፈተና ሆኗል ሲሉም  አምባሳደር ዲና አመለክተዋል።

እንደ ሀገር የገጠመን ችግር የአንድ አካል ችግር አይደለም ያሉት ቃልአቀባዩ፣ ኢትዮጵያዊያን ከምንም በላይ አንድነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

(በአሳየናቸው ክፍሌ)