መንግሥት የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመሆናችን ምስክር ነው አለ

የካቲት 12/2014 (ዋልታ) የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመሆናችን ምስክር ነው ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ያለው ዕለት መሆኑን አስታውሶ ዕለቱ የዛሬ 92 ዓመት ገደማ በኢትዮጵያዊያን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈፀመበት ቀን ነው ብሏል፡፡

ለዘመናት የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያዊያንን በኃይል በማንበርከክ ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል ያለው መግለጫው ሙከራዎቻቸውም ሳይሳካ ሽንፈት ተከናንበው ተመልሰዋል ነው ያለው፡፡

በ1888 ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የጣሊያን ጦር ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቆ መምጣቱንና ባልተለመደ ሁኔታ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ዘመናዊና ግዙፉ የጣሊያን ጦር ብርቱ ልብ እንጂ ይኼ ነው የሚባል ዘመናዊ መሳሪያ ባልነበራቸው በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ተሸንፎ መመለሱንም አስታውሷል።

ይህ ሽንፈት ለኢትዮጵያ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ድል ቢሆንም ወራሪውን ኃይል አንገት ያስደፋ የውርደትና ቅሌት ጦርነት ነበር ሲልም አክሏል።

ከዚህ አስከፊ ውርደት ለማገገምና ኢትዮጵያን ለመበቀል በወቅቱ የጣሊያን ገዥ ቢኒቶ ሙሶሎኒ ከ40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ስለመውረሩና ለጊዜዎም ቢሆን የጦር የበላይነት አግኝቶ የተወሰኑ ከተሞችን መያዙንም ያስታውሳል፡፡

ሆኖም ግን ለነፃነታቸው የማይተኙና ባርነትን የማይቀበሉ የኢትዮጵያ ልጆች ለወራሪው ኃይል የእግር እሳት እንደሆኑባቸው መንግሥት ጠቅሷል።

በተለይም በየካቲት 12 ቀን 1929 በአዲስ አበባ ስብሰባ ሲመራ በነበረው የፋሺሽቱ እንደራሴ የነበረው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ በነፃነት ታጋዮች የግድያ ሙከራ መደረጉን ተከትሎ የፋሺሽቱ ጦር ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅሞ ከ20 እስከ 30 ሺሕ የሚገመቱ ንፁሃን ዜጎች መስዋዕት መክፈላቸውን መግለጫው አክሏል።

“ምንም እንኳን የጠላት ምኞት ኢትዮጵያዊያን ዳግም ለነፃነታቸዉ እንዳይታገሉ ለማስተማር የተደረገ ቅጣት ቢሆንም እርምጃው ጀግኖቹን ይበልጥ አጠናከራቸዉ እንጂ ከነፃነት ትግላቸው ፈፅሞ ሊያስቆማቸው አልቻለም” ሲልም የመንግሥት መግለጫ ይነበባል።

“እንዲያውም ኢትዮጵያዊያን በጠላት ሲጠቁ እጅ የሚሰጡ ሳይሆኑ ይበልጥ የሚጠነክሩና እንደ ንብ አንድ የሚሆኑ፣ ለጠላት የማይመቹ ሕዝብ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡ ጭፍጨፋው ይበልጥ ጀግኖች አርበኞች ተደራጅተው ጠላትን እንዲያርበደብዱ ጉልበት ፈጠረላቸው እንጂ ተስፋ አላስቆረጣቸውም፡፡ ጠላትን እንቅልፍ ነሱ፣ ብሎም ከነአካቴዉ ከአገራችን አባረሯቸው” ሲልም ታሪክን አስታውሷል፡፡

ይህ ለጠላት የማንመችና የማንንበረከክ፣ ነፃነት ወዳድ መሆናችን ዛሬም ቀጥሏል ያለም ሲሆን ጠላት ምኑንም ያህል ቢደረጅ፣ ቢዶልት፣ ቢያሴርና ቢተባበር የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊያን ይበልጥ አንድ የመሆንና ችግርን የመቋቋም እሴት ዛሬም አገራችንን ከብተና አድኗል፤ ለጠላት ያለመንበርከክና አሸናፊነት የጋራ ታሪካችን ብቻም ሳይሆን የጋራ ባህላችን ሆኖ ለትዉልድ ተርፏል ብሏል፡፡

ይህ የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት ላልገባው ጠላት የጥንካሬያችን ምንጭ ትንግርት ሆኖበታል በማለትም
“ዘንድሮ የየካቲት 12 ሰማዕታትን ስንዘክር የጥንካሬያችን ምንጭ የሆነውን የመተባበር ባህላችንን በማጠናከር፣ አንድነታችንን ጠብቀን ዘርፈ ብዙ ጠላቶቻችንን በማሸነፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በመትጋት ሊሆን ይገባል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።