በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው ድርድር የሩሲያ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው ድርድር የሩሲያ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ለቭሮቭ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ሰርጌ ለቭሮቭ ሩሲያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳንን እንድታደራድር ግብዣ ባይቀርብላትም ያላቸውን ልዩነት በአፍሪካ ህብረት መሪነት እንዲፈታ የሩሲያ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በንግድ እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና ከግብፁ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ሰርጌ ለቭሮቭ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ለሁለት ቀናት ግብፅ ቆይተው ወደ ኢራን አቅንተዋል፡፡