ሚኒስቴሩ ለበጀት ዓመቱ ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን አስታወቀ

ግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ሐምሌ 21/2015 (ዋልታ) የግብርና ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 67 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የማዳበሪያ አቅርቦትን እንዲሁም የመኸር እና በልግ እርሻ ስራን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደሀገር የ20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንዲፈጸም ፋላጎት ቢኖርም ሀገሪቱ ያላትን የፋይናንስ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት 13 ነጥብ 67 ሚሊዮን ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት የዞረውን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ለበጀት ዓመቱ 15 ነጥብ 87 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መቅረቡንም አመልክተዋል፡፡

አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማዳበሪያ ግዢ ወጪ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህም 11 ነጥ 9 ሚሊየን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማድረጉንና 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በጅቡቲ ወደብ የሚገኘውን ቀሪ አንድ ሚሊየን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭም ተናግረዋል።

የበልግ እርሻን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንደታረሰና ከዚህም 65 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በመኸር እርሻ ደግሞ 17 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ 15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታሩ መታረሱንና ከዚህም 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በስመኝ ፈለቀ