ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 15 የማዳበሪያ መጠባበቂያ መጋዘኖች ስራዎችን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 21/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው 15 የማዳበሪያ መጠባበቂያ መጋዘኖች የሥራ እንቅስቃሴዎችን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በስድስት ከተሞች በሚገኙ የኮርፖሬሽኑ 15 መጋዘኖች ለመጠባበቂያነት የተከማቹና ከጂቡቲ ወደብ ወደ መጋዘኖቹ በመጓጓዝ ላይ የሚገኙ ኤን ፒ ኤስ፣ ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና ዩሪያ ማዳበሪያዎችን ከተሽከርካሪዎች ላይ የማራገፍ እና ህጋዊ ፈቃድ ላላቸው ተጠቃሚዎች የመጫን ሥራ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።

በዚህም ከጂቡቲ ወደብ የሚመጣ ማዳበሪያን በመጠባበቂያ መጋዘኖች በፍጥነት ለማውረድ እና ለተጠቃሚዎች ለማሰራጨት የጫኛና አውራጅ ቁጥርን መጨመር፣ ተጨማሪ መጋዘኖችን የመከራዬት ተግባራት፣ ያሉት መጋዘኖቹ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ሁኔታዎች ማመቻቸትን ጨምሮ በአንድ ጊዜ የሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች ጭነት የሚራገፍበት አሠራር መጀመሩን በመረጃው ተመላክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክፍሌ ወልደማርያምና ከፍተኛ አመራሮች በስድስት ከተሞች የሚገኙ የማዳበሪያ መጠባበቂያ መጋዘኖችን የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገም ማዳበሪያ የማውረድና የመጫን ሥራ እንዲቀላጠፍ የሚያስችል የሥራ መመሪያ መስጠታቸው ተገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ለ2015/16 የምርት ዘመን ከገዛው 14 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 11 ሚሊዮን 975 ሺሕ 320 ኩንታል (85.5 በመቶ) ከውጭ መጓጓዙንና ከዚህም ውስጥ እስከ ሐምሌ 21/2015 ድረስ 10 ሚሊዮን 838 ሺሕ 191 ኩንታል (90.5%) ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደር ዩኒየኖች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በቅርብ ቀናት ተጨማሪ 2 ሚሊዮን 9 ሺሕ 750 ኩንታል ዩሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ኮርፖሬሽኑ በየሰብል ዘመኑ ወደ ሀገር ቤት ከሚያስገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ አምስት በመቶውን ማዳበሪያ በመጠባበቂያ መጋዘኖቹ በማከማቸት ከግብርና ሚኒስቴር ፈቃድ ለሚያገኙ የክልል ዩኒየኖች፣ የሰፋፊ እርሻዎች ባለሀብቶች እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሽያጭ የማቅረብ ተልዕኮ እንዳለው ይታወቃል።