ሚኒስቴሩ በመቐለ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 50 ቶን የአልሚ ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 30/2013 (ዋልታ) – የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቐለ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል 50 ቶን የሚገመት አልሚ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከጤና እና ባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈንታ አሰፋ ተናግረዋል።

ድጋፉ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ዘይት፣ ፊኖ ዱቄት እና እንዲሁም የህፃናት አልሚ ምግቦችን የያዘ ሲሆን፣ ለህፃናትና አዋቂዎች የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትም ያካተተ መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች እርዳታውን በማሰባሰብ በመተከልና አጣዬ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ጭምር እያዳረስን እንገኛለን ብለዋል።

አሁን ለትግራይ ክልል የተሰጠው ድጋፍ ከ30 ሚልየን ብር በላይ እንደሚገመት በመግለፅ፣ እርዳታው በቀጥታ በመቐለ ከተማ በተለያዩ የመጠለያ ካምፖች ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች እንደሚውል ማስታወቃቸውን የትግራይ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ ዘግቧል።