ሚኒስቴሩ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ9 መቶ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ የሚውል 900,503,155.22 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የምግብ ምርቶችና የአልባሳት ድጋፍ አደረገ፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ተቋሙ “የህዝብን ሀብት ለህዝብ፤ ለወገን ደራሽ ወገን ነው” መርህን በመከተል የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ ለሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ለሜቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ማህበር መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
በድጋፍ አሰጣጥ ስነስርዓቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው፣ ተቋሙ ገቢን የመሰብሰብና ኮንትሮባንድን የመከላከል ተልዕኮዎች በአግባቡ እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት ስምንት ወራት 191.4 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ባጋጠሙ ችግሮች ሁሉ እጁን በመዘርጋት በኮንትሮባንድ የተያዙ እቃዎችን ለጉዳት ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመስጠት የህዝብን ሀብት ለህዝብ እያደረሰ መሆኑን የተናገሩት፣ ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት ወራት 1.3 ቢሊየን ብር በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፣ ተቋሙ ኮንትሮባንድን ከመከላከል ባለፈ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ለጉዳት የተጋለጡ ወገኖችን ሲያግዙ መቆየታቸውን አንስተው፣ ተወካዮች የተሰጠውን ድጋፍ ለሚመለከታቸው ዜጎች በጊዜው እንዲያደርሱ አሳስበዋል፡፡
በዛሬው እለት የተሰጠው ድጋፍ በህግ ማስከበር የተፈጠሩ ችግሮችን፣ የተከሰቱ ግጭቶችን፣ የጎርፍ አደጋዎች፣ የአንበጣ ወረርሽኝን፣ የእሳት ቃጠሎ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህም ለትግራይ ክልል 119.4 ሚሊየን ብር፣ ለኦሮሚያ ክልል 107.335 ሚሊየን ብር፣ ለአማራ ክልል 100.4 ሚሊየን ብር፣ ለደቡብ ክልል 89.9 ሚሊየን ብር፣ ለሶማሌ ክልል 69.03 ሚሊየን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 67.84 ሚሊየን ብር፣ ለጋምቤላ ክልል 57.14 ሚሊየን ብር፣ ለአፋር ክልል 52.144 ሚሊየን ብር፣ ለሲዳማ ክልል 51.55 ሚሊየን ብር፣ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 49.09 ሚሊየን ብር፣ ለሀረሪ ክልል 48.54 ሚሊየን ብር፣ ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 44.019 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለሜቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡