ቶታል ኢትዮጵያ 800 ሺህ ብር የሚያወጣ የሕክምና ጓንት ድጋፍ አደረገ

ቶታል ኢትዮጵያ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – ቶታል ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዝ 800 ሺህ ብር የሚያወጣ የሕክምና ጓንት ድጋፍ ለጤና ሚኒስቴር አስረከበ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉን ከቶታል ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ቲቦ ሌዢየ ተረክበዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፉ መደረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ቲቦ ሌዢየ፣ አጋርነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ወረርሽኙ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እያደረሰ ያለውን ቀውስ በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል ያከናወናቻቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

የቶታል ኢትዮጵያ የማኅበራዊ ጉዳይ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይለኢየሱስ አሰፋ የዛሬውን ጨምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል እስካሁን 21 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ በቶታል ኢትዮጵያ መደረጉን ገልጸዋል።

ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ሳኒታይዘር፣ ለአምስት የመንግስት የጤና ተቋማት የውሃ ታንከርና የመታጠቢያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

ለአራት አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች የንፅህና መጠበቂያ ሳሙናና ለኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አምቡላንሶችና ተሽከርካሪዎች የሚውል የአንድ ሚሊየን ብር የነዳጅ አቅርቦት እገዛ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፣ ቶታል ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሲያግዝ መቆየቱን አረጋግጠው፣ “ለጤናው ዘርፍ ስራዎች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ከመቆየቱም በላይ በማኅበረሰብና በተቋማት ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን አከናውኗል” ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍ የጤና ባለሙያዎችንና ተገልጋዮችን ከቫይረሱ ለመጠበቅና ወረርሽኙን ለመከላከል አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ለድጋፉ ምስጋና ያቀረቡት ዶክተር ሊያ ኮቪድ-19ን ከመከላከል በተጨማሪ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻልና ለማጠናከር ቶታል ኢትዮጵያ ትብብሩን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን አዜአ ዘግቧል።