ሚኒስቴሩ ባለፉት 10 ወራት ከ238 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰበሰቡን አስታወቀ

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት አስር ወራት 238 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰበሰቡን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለመሰብሰብ ካቀደው 242 ቢሊየን 638 ሚሊየን 828 ሺህ 218.25 ብር 238 ቢሊየን 362 ሚሊየን 300 ሺህ 842.16 ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 98.24 በመቶ ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ የሰበሰበው ገቢ በ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር የ19.77 በመቶ ወይንም የብር 39.3 ቢሊየን ዕድገት እንዳለው የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡

ገቢው የተሰበሰበው ከሀገር ውስጥ ታክስ፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ፣ ከሎተሪ ሽያጭ የተገነ የተጣራ ገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ከሀገር ውስጥ ታክስ 145.5 ቢሊየን ብር በላይ፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 92.6ቢሊየን፣ ከሎተሪ ሽያጭ የተጣራ ገቢ 193.27 ሚሊየን በላይ ተሰብስቧል።

የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ለዚህ መልካም ውጤት መገኘት ግብር ከፋዮችን፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ለነበራቸው አስተዋፅኦ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህ የጋራ ጥረትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።