አትሌት ዘውዲቱ አደራው እና አትሌት ጫላ ከተማ በግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ ሆኑ

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው 16ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት ዘውዲቱ አደራው በወንዶች ደግሞ አትሌት ጫላ ከተማ አሸናፊ ሆነዋል።

በሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ከአማራ ፖሊስ የተገኙት አትሌት ዘውዲቱ አደራው እና እናትነሽ አላምረው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተወከለችው አትሌት መሰረት ጎላ 3ኛ ሆና ውድድሩን ማጠናቀቅ ችላለች።

በወንዶች የግማሽ ማራቶን ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ የተገኘው አትሌት ጫላ ከተማ ውድድሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ ከፌደራል ማረሚያ የተወከለው አትሌት ተሰማ መኮንን 2ኛ አንዲሁም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተገኘው አትሌት ሀብታሙ አብዲ 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ከሁለት ክልሎች 12 ክለቦች እና ተቋማት እንዲሁም በግል የሚወዳደሩ አትሌቶችን ጨምሮ በወንድ 190፣ በሴት 96 በድምሩ 286 አትሌቶች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል።