ሚኒስቴሩ የሰላም ስምምነቱ የቱሪዝም ኢኮኖሚን እንደሚያነቃቃ አስታወቀ

ታኅሣሥ 21/2015 (ዋልታ) ከሰላም ስምምነቱ ማግስት የሚከበረው የገናና የጥምቀት በዓል ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ እንደሚያደርግ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የግብይትና ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ኃይማኖታዊ ፌስቲቫሎች የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ፣ የውጭ አገር ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲጎበኙ ለማነሳሳት እና የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ያስችላሉ ብለዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲጎበኙ ከሚጋበዙባቸው ወቅቶች አንዱ የገናና የጥምቀት ፌስቲቫል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለፈው ዓመት በገናና በጥምቀት በዓል ከመቶ ሺሕ በላይ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ፌስቲቫሎችን ተካፍለዋል፣ የቱሪስት መዳረሻዎች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት እንደ አገር ብዙ ፈተናዎች ባሉበት የገናና የጥምቀት ፌስቲቫል ተከብሯል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዘንድሮው የሰላም ስምምነት በተደረገበት ማግስት የሚከበሩ የጥምቀትና የገና ፌስቲቫሎች በርካታ ቱሪስቶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ብለዋል።

ዳያስፖራውና ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ቱሪስቶች ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጎበኙበት እድል ከባለፈው ዓመት የተሻለ አጋጣሚ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ የቱሪዝም ሀብት የሚንቀሳቀሰው በቱሪስት መስብ ቦታዎች የሰዎች እንቀስቃሴ ሲኖር ነው ብለዋል።

ከአገር ውስጥም ከውጭም ሰዎች መጥተው ጉብኝት የሚያደርጉበት ሁኔታ መፈጠሩ የቱሪዝሙን ኢኮኖሚ በማሳደግ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡