በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ፈጥነው ሊጠናቀቁ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

ታኅሣሥ 21/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች በተገባው ውል መሰረት መጠናቀቅ እንደሚገባ አሳሰበ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን ጭዳ-ጅማ እና ጎሬ-ቴፒ-ማሻ እየተሰሩ ያሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

ከአመራሮች፣ ከፕሮጀክት ፅሕፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ ከኮንትራክተሮች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የመንገድ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት በሚሰጥበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

በተደረገው ውይይት ላይ የቋሚ ኮሚቴው አባል አልማዝ አሳሌ የተጀመሩ የመንገድ መሰረተ-ልማቶች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ የየፕሮጀክት ተቋራጮች፣ የፕሮጀክት አማካሪዎች እንዲሁም የአካባቢው አመራርና ህብረተሰቡ ተቀራርበው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት ውግንናው ለሕዝብ መሆን እንዳለበት አዉስተዉ ካሳ ተከፍሎ ያልተነሱ ንብረቶች በአካባቢው አመራር እገዛ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባና ለመንገድ ግንባታ አስቸጋሪ የሆኑ መሬቶች ተጠንተው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥባቸውም የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማ ቅርንጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ልሳነወርቅ ክፍሌ ከጅማ ጭዳ እየተሰራ ያለው መንገድ የዘገየ መሆኑንተናግረዋል፡፡

የወሰን ማስከበር ችግር አየር ንብረት የክፍያ መዘግየት የግንባታ ግብኣቶች እና የማሸነሪዎች እጥረት ለመንገዱ መዝግየት ምክኒያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡