ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) የኮቪድ 19 ክትባት ለኅብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር የገለፁት ሚኒስትሯ ከመከላከል ስራዎች አንዱ የሆነው የኮቪድ ክትባት ተደራሽነትን የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ከሚሰጡት ሶስት የክትባት ዓይነቶች በተጨማሪ የፋይዘር ክትባት መሰጠት መጀመሩንም ገለፀዋል።
ከትላንት ኅዳር 6 ጀምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት ጀምሮ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እንደሚሰጥ ያመለከቱት ዶ/ር ሊያ በ65 ከተሞች የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 3 ሚሊየን 672 ሺሕ 900 ሰዎች የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን የጤና ሚኒስቴር ትላንት ያወጣው ዕለታዊ መረጃ ያመለክታል።
በሚኪያስ ምትኩ