ሚኒስትሩ በአልሸባብ ጥቃት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሃዘን ለሶማሊያ መንግስትና ህዝብ ገለፁ

የካቲት 6/2016 (አዲስ ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴ አሸባሪው አልሸባብ ከሰሞኑ በሶማሊያ በፈፀመው የሽብር ጥቃት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

አምባሳደር ታዬ ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት በሽብር ቡድኑ ጥቃት ምክንያት በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት እና አካል ጉዳት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እንዲሁም በራሳቸው ስም የተሰማቸው ጥልቅ ሃዘን ለሶማሊያ መንግስት እና ህዝብ ያስተላለፉት ሚኒስትሩ በልምምድ ወቅት ወታደራዊ መኮንኖችን ኢላማ በማድረግ የተፈፀመውን ጥቃት የወንጀል ተግባር ነው ብለዋል።

የወንጀል ተግባሩን ኢትዮጵያ በፅኑ እንደምታወግዘውም በመልዕክት አስታውቀዋል።

ጥቃቱ አልሸባብ የሽብር ቡድን በሶማሊያ እና በክፍለ አህጉሩ ደህንነት አደጋ መደቀኑን በግልፅ ያረጋገጠ መሆኑን በመግለፅ የአካባቢው ሃገራት በፀረ ሽብር የሚያደርጉትን ትብብር ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሶማሊያን ሰላም እና ደህንነት በጋራ ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ትብብሯን አጠናክራ በቁርጠኛነት እንደምትቀጥልም መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።