አማርኛ ቋንቋ በአፍሪካ ሕብረት የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲካተት ተጠየቀ

የካቲት 6/2016 (አዲስ ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀ ሥላሴ አማርኛ ቋንቋ በአፍሪካ ሕብረት የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲካተት ጠየቁ።

የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ታየ የመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር አማርኛን ጨምሮ በአራት ቋንቋዎች የተፈረመ እንደነበር አስታውሰው አማርኛ ቋንቋ የሕብረቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ሀሳብ አቅርበዋል።

እ.አ.አ አቆጣጠር በ1963 በአዲስ አበባ የተፈረመው ቻርተሩ በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች ነበር።

አሁን የአፍሪካ ሕብረት ከ6 በላይ የስራ ቋንቋዎች ያሉት ሲሆን አማርኛ ቋንቋም እንዲካተት በ44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ ተጠይቋል።