ሚኒስትሩ የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን የልማት ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጠየቁ


የካቲት 19/2016 (አዲስ ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያደረገ ያለውን የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ።

ሚኒስትሩ ከባንኩ ዋና ዳይሬክተር ጆናታን ንዛኮሬራ ጋር ተወያይተዋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ያደነቁት ሚኒስትሩ በሀገሪቱ እየተተገበረ ላለው ሪፎርምና የአቅም ግንባታ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍም አመስግነዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን በማስተባበርና የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን በማገዝ እያበረከተ ያለውን ሚና አድንቀው ባንኩ በኢትዮጵያ ያለውን የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ባንኩ ለኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት፣ የውኃ፣ የግብርናና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማት ስለሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ድጋፎች አብራርተዋል።

ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች በቀጣይ ጠንካራ ግንኙነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ወቅታዊ ውይይቶችን ለማድረግ መስማማታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።