ለአዲስ ዋልታ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሽልማትና እውቅና ተበረከተላቸው

የካቲት 19/2016 (አዲስ ዋልታ) በ13ኛው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚዲያ ካፕ አሸናፊ ለሆነው የአዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ተጫዋቾች የገንዘብ ሽልማትና እውቅና ተበረከተላቸው።

ለእያንዳንዳቸው የቡድኑ ተጫዋቾች 20 ሺሕ ብር የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ ሀሰን የእውቅናና የገንዘብ ሽልማቱን በውድድሩ ለተሳተፉ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች አበርክተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በመርኃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ውጤቱ እንደ ተቋም ኅብረታችንን ያሳየንበት በስራችንም ትልቅ ስኬት እያስመዘገብንበት መሆኑን የሚገልፅ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከኳሱ ጋር ተያይዞ እንደ ተቋም የቡድን ስራ የታየበት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ያሸነፍነው ኳሱን ብቻ አይደለም መሸነፍን ጭምር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሽልማት የተበረከተላቸው ተጨዋቾች በሰጡት አስተያየት ባስመዘገቡት ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው የተደረገላቸው ማበረታቻ በቀጣይ ከዚህ በላይ ተቋሙን ለማገልገል እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

በተቋሙ በሰራተኞች መካከል የቤተሰባዊነት ስሜት እንዲፈጠር እየተሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ መሆኑንም አመልክተዋል።

በ13ኛው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚዲያ ካፕ አዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ሪፖርተር ጋዜጣን 3ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ ይታወሳል።

በውድድሩም የ13 ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 32 ሚዲያዎች በተካተቱበት ውድድር ከ450 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ተመላክቷል።