ሚኒስትሩ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር ገለጹ

ሐምሌ 7/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግብጽ ካይሮ በተካሄደው ‘የሱዳን ጎረቤት አገራት ጉባዔ’ የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ ቆይታቸው ሦስት አበይት ተግባራትን በተሳካ መልኩ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመጀመሪያም ጠቅላይ ሚኒስትር መሰረተ-ልማት የተሟሉለት ዘመናዊውን አዲሱ ካይሮን መጎብኘታቸውን ጠቁመው በዚህም የኃይማኖት ተቋማት፣ ሙዚየምና ሌሎች ሥፍራዎችን መጎብኘታቸው አንስተዋል፡፡ ጉብኝታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ የሚሆን ልምድ መቀመራቸውንም ተናግረዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የተሳካ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የሁለትዮሽ ስብሰባ አገራቱ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከሥምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

አገራቱ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ቀጣይ የትብብር ዘርፎች እንዲሁም በአካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸውንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት ያደረገ ትብብር ለሁለቱ አገራት ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅምና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ ከመግባባት መድረሳቸውን አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በመተማመን መንፈስ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ለቀጣናው ልማት ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል ነው ያሉት።

ይህንን ለማድረግ ሁለቱ አገራት ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በመከባበርና በሰጥቶ መቀበል መርህ አጋርነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መወያየታቸውን ተናግረዋል።

የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት በግብጽ ካይሮ የመከሩት የጎረቤት አገራት መሪዎች ተፋላሚ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በችግር ላይ የሚገኙ ሱዳናዊያን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙና ሁለቱ ኃይሎች ሁሉን አቀፍ ውይይት በፍጥነት እንዲጀምሩ መሪዎቹ ከሥምምነት መድረሳቸውንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህም ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የሱዳን ሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ መከናወን እንዳለበት መሪዎቹ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፋቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የሱዳን ችግር እንዲፈታ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ጽኑ አቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውንም አብራርተዋል።