አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦንብ መላኳ ተገለጸ

ክላስተር ቦንብ

ሐምሌ 7/2015 (ዋልታ) አሜሪካ ለዩክሬን ከ120 በላይ አገራት የተከለከለውን ክላስተር ቦንብ መላኳ ተገለጸ፡፡

አሜሪካ ከሰሞኑ ክላስተር ቦንብ ለዩክሬን ለመስጠት እንደምትፈልግ መግለጿን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቃውሞዎች በርትተው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የጦር መሳሪያው ዩክሬን እጅ መግባቱ ተነግሯል፡፡

የዩክሬን ባለስልጣናት ክላስተር ቦንቡን የምንጠቀመው የጠላት ጦር በተከማቸባቸው ውስን አካባቢዎች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የደቡባዊ ዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ ቫለሪን ሸርሸን መሳሪያዎቹን በሩሲያ ግዛት ውስጥ አንደማይጠቀሙ ገልጸው ነገር ግን የሩሲያ ጦር በብዛት የተከማቸባቸውን ቦታዎች ምሽግ ለመስበር ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ክላስተር ቦንቦቹ ጥቅም ላይ የሚውሉ ከሆነ ምላሹ ተመሳሳይ እንደሚሆን ማስጠንቀቋን አልጃዚራ ዘግቧል፡፡

ይህን የአሜሪካን ድጋፍ ካናዳ፣ ስፔን እና እንግሊዝ የክላስተር ቦምቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ስምምነት የጣሰ ነው በሚል ተቃውመውታል፡፡

ክላስተር ቦንብ በአየር የሚጣል ወይም ከመሬት የሚተኮስ ፈንጂ ሲሆን አንዱ ቦንብ በውስጡ በርካታ ትናንሽ ቦንቦችን የያዘ አደገኛ መሳሪያ ነው፡፡ ክለስተር ቦንቡ ሲተኮስ ትናንሾቹ ቦንቦች ከተያዙበት ተተኳሽ በመውጣት በሰፊ መሬት ላይ ተሰራጭተው የአንድ የእግር ኳስ ሜዳ ስፋት ባለው መሬት ላይ ያለን ኢላማ የማውደም አቅም እንዳላቸውም ተመላክቷል፡