ማይንድ ኢትዮጵያ 1 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን የሚያሳትፍ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – ማይንድ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን የሚያሳትፍ መድረክ ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

መድረኩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ማይንድ ኢትዮጵያ የስምንት ሀገር በቀል ድርጅቶች ጥምረት መሆኑን ገልጸው፣ ሀገራዊ የምክክር መድረክ በማመቻቸት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

ድርጅቶቹም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣፤ የሀሳብ ማዕድ፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ፣ የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያንስ ፎር ኢንክሉሲቭ ዳያሎግና የሰላም ሚኒስቴር ናቸው።

ማይንድ ኢትዮጵያ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በአደረጃጀታቸው አማካኝነት በሀገር ደረጃ አንኳር የሚባሉ አጀንዳዎች ለውይይት እንዲቀርቡ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስታውቋል።

ከአርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን፣ ከአሰሪዎች ኮንፌደሬሽን፣ ከአካል ጉዳተኞች ኮንፌደሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት፣ ከመምህራን ማህበር፣ ጡረታ ከወጡ ኢትዮጵያውያን፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሁሉም ክልሎች የታችኛው ማህበረሰቦች እና ከመንግስት ሰራተኞች ሀገራዊ አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱም ተጠቁሟል።

በቅርቡም ከክልሎችና ከዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት ላይ ይገኛል ተብሏል።

አጀንዳዎቹን ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ሀገራዊ ምክክሩን ሊመሩ የሚችሉ ሰዎችን ጥቆማ የተቀበለ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ግለሰቦችን ዝርዝር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመቀበል ላይ እንደሚገኝ አመላክቷል።

በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ አካላት ስብጥር እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፤ ፆታ፣ እድሜ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ኃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ክልል፣ ትምህርት ዝግጅትና የመሳሰሉትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ይሆናልም ተብሏል።

በውይይቱ ወቅት አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን አስማሚና አስታራቂ የሚሆኑ የኃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰላም እናቶች እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች በጥንቃቄ ተመርጠው የማሸማገል ሚና እንዲጫወቱ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡

ማይንድ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያጠናቅቅ የሀገራዊ ምክክሩን በይፋ የሚያከናውን ሲሆን፣ ከሀገሪቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ዜጎች መሳተፍ እንዲችሉ ታቅዶ እየተሰራ ነውም ተብሏል።

(በደረሰ አማረ)